እውነተኛ ፍቅር እንዳለ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ያ በእናንተ ላይ ተስፋ የማይቆርጥ፣ ሁልግዜ ሚደግፋችሁ፣ ስትበረቱ ብቻ ሳይሆን በድካማችሁና በውድቀታችሁም ሚጠብቃችሁ፣ ያ በነዛ ክፉ ቀናት እጁን ዘርግቶ ከጉያው ሚያስገባችሁ፤ ያ ፍቅር ፡፡
በዚህ ዘመን ስለ ፍቅር ብዙ ልክ ያልሆኑ ምልከታዎች አሉ፡፡ ብዙዎቻችን ፍቅርን በማያዛልቁ በምንለዋውጣቸው መልእክቶች፤ በምናሳያቸው ቶሎ ሊጠፉ በሚቸሉ ገጽታዎችና የመሳስሉት ቀይረናቸዋል፡፡ነገሮች መልካም በሆኑበት ጊዜ ይህን ፍቅር ማግኘት ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ህይወት በሚጨልምበት ጊዜ ይህ ፍቅር ከእጃችን ተኖ ይጠፋል፡፡ በዚህ ምክንያት እንዲህ ብላችሁ እንድትጠይቁ ያደርጋችኅል፦ነገሮች በሚቀየሩ ግዜ ጥሎኝ የማይሄድ ከኔው ጋር የሚቀር ፍቅር ይኖር ይሆን?
መልካሙ ዜና ግን ይህ ነው፡፡ ያ አይነት ፍቅር አለ፡፡ ከእናንተ ጋር የሚሆን ብቻ ሳይሆን እናንተንም የሚፈልግ፣ ጽኑ፣ ፍጹም፣ የማይናወጥ እንደሁም ከሁኔታ ውጪ የሆነ ያ ፍቅር በእርግጥ አለ፡፡ እናንተ ባላችሁበት የትኛውም ሁኔታ የሚቀበላችሁ፤ያ ፍቅር በእርግጥ አለ፡፡ እናንተ ባላችሁበት የትኛውም ሁኔታ የሚቀበላችሁ፤ እሱ ፍቅር አለ፡፡ የሚያስገርመው ይህ ፍቅር ፍጹም ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን እንደ እኛ ላሉት ነው፡፡ይህ ፍቅር እውነት ነው እርሱም የእግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡
ፍቅር ደካማ በሆነበትና በሁኔታዎች በሚወሰንበት በዚህ ዘመን ልዩ ሆኖ የሚገኘው የእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ እሱም በእናንተ ስኬት፤ውድቀትና ሁኔታ ላይ አይመሰረትም፡፡ ይልቁንም ይህ ፍቅር ከሁኔታዎች ውጪ በሆነ መንገድ የተገለጠ ነው፡፡ እሱም እጅግ ጥልቅ የሆነና በመከራችን ግዜ የሚረዳን፤ በሚያስገርም ጸጋው የከበበንና በማይነጥፍ ተስፋ የሚያጸናን ነው፡፡
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ፍቅር ከመሆኑ የተነሳ እናንተን በማበጀት ውስጥ ፍቅሩን ገልጿል፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር የመልካምነቱና የቸርነቱ መጨረሻ መገለጫ ነው፡፡ እርሱ በፍቅሩ እጅግ ታጋሽ ነው፤ ፈጽሞ አይቸኩልም ነገር ግን በመልካምነቱ እየጠበቀን በማይገባን ጸጋ ይባርከናል፡፡ አስቡት እስቲ ምን ያህል ግዜ እንደወደቅን፤ ምን ያህል ግዜ ከሱ እንደራቅን እሱ ብቻ አይደለም ሰዎች በኛ ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ፡፡ ደስ የሚለው ግን እግዚአብሄር በእኛ ተስፋ አለመቁረጡ ነው፡፡ እግዚአብሄር በብርታታችን ግዜ የሚወደን አምላክ ብች ሳይሆን በድካማችን፤ በውድቀታችንና ጸጋው በሚያስፈልገንም ግዜ የፍቅር እጁ ሁል ጊዜም እንደተዘረጋልን ነው፡፡
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ ዮሐንስ 3:16 “እግዚአብሄር አለምን እንዲሁ ወዶአል…”
አስባችሁት ታውቃላችሁ ከእኛ እውቀት በላይ የሆን፤መጨረሻ የሌለው፤እጅግ ታላቅ ፍቅር? ስለመወደድ ስናወራ ለማለት ያክል ብቻ ሳይሆን ምን ይህል የእግዚአብሄር ፍቅር ትልቅና የማይናወጥ አንደሆነ ለማስታወስ ጭምር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ዝም ብሎ ስሜት ሳይሆን የሚደንቅ እንዲሁም ሁል ግዜ የምናገኘው ፍጹም ነጻና መልካም የሆነ ስጦታ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ይህን ፍቅር ለማግኘት ምንም ማረግ ሳይጠበቅብን እንዲሁ ፍጹምና ንጹህ ከሆነው ከእግዚአብሄር ዘንድ የተቀበልነው መሆኑ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሁል ግዜ እግዚአብሄር ምን ያህል እንደሚወደኝ ሳስብ በደስታ እሞላለው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ፍቅር በደንብ ሲገባችሁ እናንተጋር ያለውን ብርሃን ለሌሎች ታካፍሉታላችሁ እንጂ በፍጹም ይዛችሁት አትቀመጡትም፡፡
“…አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ…”
እግዚአብሄር ምን ያህል ከርሱ ርቀን እንደሄድን፤ እንደጠፋንና ህይወታችን በብዙ ችግር ውስጥ እንዳለ ያውቃል፡፡ የሚገርመው ግን እንደዛ እየበደልነው ፍቅሩን ከኛ አለመከልከሉ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ውድ የሆነውን አንድያ ልጁን እየሱስ ክርስቶስን ሰጠን፡፡ ምን አይነት ፍቅር ነው? ታዲያ በዚህ ልዩ በሆነው ፍቅር እንዴት አለመለወጥ ፣አለመነካት እንችላለን? ክርስቶስ ስለ ፍቅር ብቻ አላወራም፡፡ ይልቁንም ኖሮታል፡፡ እሱ እውነተኛና ከራስ በላይ የሆነውን ፍቅር አሳይቶናል፡፡ የፍቅርን ጥግ የገለጠውም ህይወቱን ለእኛ አሳልፎ በመስጠቱ ነው፡፡ የሚገርመው ክርስቶስ ነብሱን አሳልፎ የሰጠው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ ጠፍተን ለነበርነው ለእኛ ለሁላችን መሆኑ ነው፡፡
በዮሐንስ 15:13(አመት)
እየሱስ እንደዚህ ብሎ ነበር “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡” የሚገርመው እውነት ግን እየሱስ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠው እሱን ገፍተው ሊሄድ ለሚችሉ ሰዎችና እያደረገ ያለውን ነገር ላይረዱ ለሚችሉ ሰዎችም ጭምር መሆኑ ኑው፡፡ ይህ ፍቅር እኛ ከምናስበው በላይ እጅግ ታላቅ የሆነ፤የማይናወጥና በጸጋ የተሞላ ነው፡፡
ሌላው የሚደንቀው ነገር ደግሞ የክርስቶስ ፍቅር የሚመነጨው ከራሱ መልካምነት መሆኑ ነው፡፡ እኛ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥም ብንሆን እንኳ ይህ ፍቅር ፈጽሞ አይለወጥም፡፡
“…በእርሱ የሚያምን ሁሉ…”
ይህ የፍቅር ጥሪ ለሁሉም ክፍት የሆነ ነገር ግን በክርስቶስ ለማመን ፈቃደኛ የመሆን ውሳኔን የሚፈልግ ነው። ክርስቶስን ስናምን በእርሱ ላይ ተደግፈን ከርሱ ዘንድ የሆነውን የዘላለምን ህይወትንና ጸጋን እንቀበላለን፡፡ ክርስትና ማለት እኛ በራሳችን ሰርተን የምናገኘው ሽልማት ሳይሆን ከክርስቶስ የምንቀበለው ስጦታ ነው፡፡ ያም በልጁ በክርስቶስ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ህብረት ነው፡፡
“…የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ…”
የእግዚአብሄር ፍቅር ደስ የሚያሰኘውን ተስፋ አምጥቶልናል፡፡ እርሱም እምነታቸውን በክርስቶስ እየሱስ ላደረጉ የዘላለም ህይወት ዋስትና ነው፡፡ ሃጥያት ከእግዚአብሄር አርቆን እና አጣልቶን ነበር፡፡ ነገር ግን በክርስቶስን መስዋዕትነት አማካኝነት ከእግዚያብሄር ጋር ተታረቅን፣የሃጥያታችንም እዳ ተከፈለ፡፡ በዚህም ምክንያት የዘላለምን ህይወት ተቀበልን፡፡
ሮሜ 6:23(አመት)
የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።
ትንቢተ ኤርሚያስ 31:3(አመት)
እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ፥ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ።
ይህ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የገባው የማይናወጥና ዘላለማዊ ኪዳን ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ፍቅር ለእስራኤላውያኖች ብቻ ሳይሆን ለእኛም ፤ ለእናንተም፤ ለሁላችንም ጭምር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በጊዜ የማይወሰን፤ ለትውልድ ሁሉ የሚሆን ፈጽሞ የማይወድቅ ነው፡፡ በታላቅ ጸጋውና ፍቅሩ እስራኤልን የወደደው እግዚአብሔር ዛሬ እኛንም በማይለወጥ ፍቅሩ ይወደናል፡፡ ፍቅሩ ሁልጊዜ እኛን ለመመለስ ዝግጁ ነው፡፡ ስለዚህም ሁልግዜ ይህን አስታውሱ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር ከእኛ የራቀ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከእኛ ጋር ያለ ሁልግዜ የሚደግፈንና የሚጠብቀን ነው፡፡ ታማኝነቱ ደግሞ የጽናታችንና የተስፋችን መሰረት ነው፡፡
እየበደልነው እንኳን እግዚአብሔር ለምድነው የሚወደን ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ እግዚአብሔር ፍቅር ነው የሚል ይሆናል፤ፍቅር ማንነቱ ነዉ።
የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ድርጊትና ማንነት ላይ የሚመረኮዝ ሳይሆን ከማንነቱ የሚገኘ ነው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳ ለእኛ ያለው ፍቅር አይቀየርም፡፡ እየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፡9 ያረጋገጠልን ይሄንን ነበር ”አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ።” ነበር ያለው፡፡ ይህ የሚያሳየን የእግዚአብሔር ፍቅር ፈጽሞ እንደማይወድቅና የማይለወጥ እንደሆነ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመኖር ስንወስን እራሳችንን በክርስቶስ ፍቅር ወስጥ ተተክለን እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ደግሞ በመከራ ውስጥ በሰላምና በደስታ ጸንተን እንድንታገስ ያደርገናል፡፡
በብዙ የህይወት ውድቀት፤ ስህተትና ትግሎች ውስጥ ሆኜ እንኳ ምን ያህል እግዚአብሔር እንደወደደኝ ሳስብ የእግዚአብሔር የምህረቱ መገለጫ መሆኔን ማሰብ ያበረታኛል፡፡ የማይገባን ሆነን እንኳ ሳለ ህይወቱን በፈቃዱ ለሁላችን ሰጠ፡፡ በእውነት ምንኛ የእግዚአብሔር ፍቅር ከእኛ መረዳት በላይ ነው፡፡
የሗላ ታሪካችሁ ምንም ቢሆን፤ የተሸከማችሁት ቀንበር ቢከብድም፤ ሃጥያተኞች እንደሆናችሁ ቢሰማችሁም የእግዚአብሔር ፍቅር ግን አይለወጥም፡፡ እንደዛው እንዳላችሁ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ኑ፡፡ እየሱስ በማቴዎስ 11:28 እንደዚህ ብሎ ነበር የተጣራው ” እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” ነበረ ያለው፡፡ እሱ ፍጹም እንድትሆኑ ሳይሆን የሚፈልገው ማንነታችሁን ይዛችሁ ወደርሱ እንድትመጡ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ለምንድነው የሚበልጠው የእግዚአብሔር ፍቅር እያለ ሀሰት የሆነውን የዚህን አለም ፍቅር ፍለጋ የምትኳትኑት? ህይወቱን ለእናንተ የሰጠው ያ እርሱ እጆቹን ዘርግቶ በፍቅር እንዲህ እያለ እየጠበቃችሁ ነው፡፡ “ወደ እኔ ኑ፤ እኔ በዚህ ያለሁት የእናንተን ልብ ለመፈወስ ፤ የጠፋውን ማንነታችሁን ለመመለስ፤ የማይጠፋውን ፍቅሬን ልሰጣችሁ ነው፡፡ እናንት የእኔ ናችሁ፤ እኔም የእናንተው ነኝና ይህን ፍቅር ተቀበሉ፡፡”