← ግብዓቶች 6 ደቂቃ ንባብ
Read in English ↗
ታህሳስ 27, 2017

በእምነት የሚደረግ ጉዞ

ክብሩ አበበክብሩ አበበ
cover image

መጽሐፍ ቅዱስን ባጠናሁ ቁጥር የሚያስደንቀኝ ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈው በአላማ መሆኑ ነው፡፡ ሀሳቡም ደግሞ የሚገኘው ጠለቅ ባለ ጥናት ውስጥ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ብዙ ባሳለፍን ቁጥር እነዚህ በሚደንቁ የአጻጻፍ ስልትና ውቅር የተጻፉትን የእግዚአብሔር ሀሳቦች በደንብ እያጣጣምን እንመጣለን፡፡ ይህም የአጻጻፍ ውበት በስፋት በ 1 ቆሮንቶስ 13 ላይ በደንብ ይስተዋላል። ፍቅር አይቀናም፤ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ የሚያስደንቅ በዛውም ልክ ለመኖርብዙ ትጋትን የሚጠይቅ እውነት ነው፡፡


1 ቆሮንቶስ 13:13(አመት)

“እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።”


ስለእምነት ስናወራ በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ እምነትን ያስቀደመው በአጋጣሚ አይመስለኝም፡፡ ይህ ማለት ግን አንደኛው ከሌላኛው ይበልጣል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እምነት በክርስትና ጉዞ መጀመሪያ የሚመጣ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ስለ እምነት በምናወራበት ግዜ የአባታችን አብርሃም ህይወት ጥሩ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔር አብርሃምን ወደማያውቀው ምድር ሲጠራው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ህብረት ለመጀመር ምክንያት የሆነው የአብርሃም እግዚአብሔርን ታዞ ለመውጣት የነበረው እምነት ነው፡፡ አብርሃም እግዚአብሔር ለጠራው ጥሪ መታዘዙ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረው ህብረት የመጀመሪያ እርምጃ ነበር፡፡

ማመን ወይስ እርግጠኛ መሆን

ስለ እምነት(faith) ስናወራ እርግጠኛ ስለመሆንም(trust) አንድ ላይ ማንሳት አለብን፡፡ እምነትና እርግጠኛ መሆን ሁለቱም ተመሳሳይ ሀሳብ ቢኖራቸውም የተወሰነ ልዩነት ግን አላቸው፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆን ማርቆስ 4 ላይ ያለውን ሀሳብ እንይ፡፡ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን አስተምሮ ከጨረሰ በሗላ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በመሆን በታንኳ መሻገር ጀመሩ፤ በመሻገር ላይ ሳሉ ብርቱ አውሎነፋስ ተነሳ ታንኳይቱ መናወጥ ጀመረች፡፡ ደቀመዛሙርቱም ክርስቶስን ቀስቅሰውት “ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት ክርስቶስም ተነስቶ እንዲህ የምትፈሩት ለምንድነው? እንዴትስ እምነት(faith) የላችሁም አላቸው፡፡ በዚህ ስፍራ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ያለው ለምን እምነት ጎደላችሁ እንጂ ለምን በኔ እርግጠኛ (trust)አልሆናችሁም አላላቸወም፡፡ ምክንያቱም እርግጠኛ መሆን ማለት በተግባር የተገለጠ እምነት ማለት ነው፡፡


በተመሳሳይ ይስሀቅ ከተወለደ በሗላ እግዚአብሔር አብርሃምን ባዘዘው መሰረት አብርሃም ይስሀቅን ለመሠዋት ወደ ሞርያም ሄዷል፡፡ አብርሃም በልጁ ላይ ለመጨከን በግዜያት መካከል የዳበረ እምነት ያስፈልግው ነበር፡፡ አብርሃም እድሜው 99 እያለ እግዚአብሔር ተገልጦለት ኤልሻዳይ ፡-ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆን ነግሮት ነበር፡፡ ይህንንም ደግሞ ሙት ከሆነው ከአብርሃም ሰውነት ልጅን በመስጠት አረጋግጦለታል፡፡ አብርሃም የነበረበት ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል የሚፈጸምበት ባይመስልም፤ አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ መደገፉን አላቆመም ነበር፡፡ ምክያቱም በእግዚአብሔር ሁሉ ቻይነት ያምን ስለነበር ነው፡፡ የዕብራዊያን ጸሀፊ በዕብራዊያን 11፡9 ላይ የአብርሃም በእምነቱ መጽናት የእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ነበር ይለናል፡፡


ዕብራውያን 11:19(አመት)

“..እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው።”


የሚገርመው አብርሃም እምነቱ የነበረው በራሱ በእግዚአብሔር ላይ እንጂ እግዚአብሔር በሚሰጠው ነገር ላይ አልነበረም፡፡ የአብርሃም በእግዚአብሔር ላይ የነበረው መተማመን እየጨመረ የሄደው በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት የተነሳ ነበር፡፡ እምነት ማለት በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ያለን መደገፈ የሚያድግበት መሠረት ማለት ነው፡፡ መተማመን ማለት ነገሮች እንኳን የሚሆኑ በማይመስሉበት ግዜ እግዚአብሔር እንደሚያረጋቸው በማመን መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ሁሉን ነገር በሚችል በእግዚአብሔር ላይ ጥልቅ የሆነ እምነት ካለን እግዚአብሔር እንደሚሰራ እርግጠኛ መሆን(መተማመን) እንችላለን።

የሚያድግ እምነት

አንዳንድ ግዜ ሰዎችን ለማመን ስሞክርና ሲያቅተኝራሴን አገኘዋለሁ፡፡ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር ሰው ማመን እየፈለገ እንዴት ያቅተዋል የሚለው ነው። አሁን የገባኝ ነገር ግን ለማመን መፈለግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ እና ልባችን ለማመን ሰዎች እንደማይጎዱን እርግጠኛ መሆን መፈለጉን ነው። ብዙ ግዜ ደግሞ ችግር የሚፈጥረው ያለምንም እምነት መሰረት በሰዎች እርግጠኛ ስንሆን ነው፡፡


እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ህብረት የሚሰራው በዚህ አይነት መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሔርንም በአንድ ለሊት አምነነው ቁጭ አንልም፡፡ ሲጀምር እግዚአብሔርን የማናምነው ከሆነ በእርሱ ላይ መደገፍና መታዘዝ ያቅተናል። ስለዚህ እግዚአብሔርን ለመደገፍ በእርሱ ማመን አለብን፡፡ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ህይወቴ ሰሞን ከሰዎች ጋር የነበረብኝ ያለመተማመን ችግር በእኔና በእግዚአብሔር መካከል ወዳለው ህብረት አምጥቼው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን ማመን ይከብደኝ፤ ባለማመኔም እንደማሳዝነው ይሰማኛል። ይህም የሆነው ስለ እግዚአብሔር ማንነት ትክክለኛ የሆነ መረዳት ስላልነበረኝ ነው፡፡ እውነታው ግን እምነት ጊዜ መፈለጉ ነው። እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ባለን የለትተለት ህብረት ውስጥ እየዳበረ፤ ህይወታችንን በእግዚአብሔር መልካምነት ውስጥ እንድናይበት የሚያደርገን ነው። በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ግን እምነት ጊዜ ይፈልጋልና እግዚአብሔር ይታገሰናል ፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜ ባሳለፍን ቁጥር ስለሱ በደንብ እያወቅን፤ በእርሱ ላይ ያለን እምነት እየጨመረ ይመጣል።

በእምነት መመላለስ

ለክርስትና ህይወታችን ዋነኛው መሠረቱ በእምነት መመላለስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በብዙ ቦታዎች ይህንን ያስታውሰናል፡፡ ለምሳሌ 2 ቆሮንቶስ 5:7 “ ምክንያቱም የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።” ፤ ምሳሌ 3:5 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ::” የእግዚአብሔር መንፈስ ካልረዳን በቀር፤ እኛ ሰዎች መልካሙን ከክፉ ለመለየት የማንችል ምስኪን ፍጥረቶች ነን፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ሎጥ ነው፡፡ አብርሃምና ሎጥን ከመለያየታቸው በፊት የወደደውን ቦታ እንዲመርጥ እድል በሰጠው ግዜ ሎጥም ደስ ያሰኝውን ቦታ መረጠ፡፡


ዘፍጥረት 13:10(አመት)

“ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብፅ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው።”


ሎጥ በራሱ መረዳት የሚደገፍና በማየት ብቻ የሚመላለስ ሰው ነበር፡፡ መጨረሻውም ሰዶምና ገሞራን እንደ እግዚአብሔር ገነት መመልከት ሆነ፡፡ እኛም ብንሆን በእምነት ለመመላለስ እግዚአብሔርን ካልታመንን እግዚአብሔር የማይከብርበትን ስፍራ እንመርጣለን፤ እግዚአብሔር የሰጠን ነፃነት ከአመፅ ጋር ይምታታብናል።እምነት ማለት የህይወት ምልልስ ነው፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በቃሉ አማካኝነት እምነታችን እንዲያድግና በእምነት መመላለስ እንድንችል ይጋብዘናል፡፡

በህይወት መንገድ ላይ እምነት ይረዳናል!

ስለ ቡና የምወደው አንድ ታዋቂ አባባል አለ” ህይወት ከባድ ሊሆን ይችላል ቡና ግን የተሻለ ያደርገዋል፡፡”(life happens coffee helps)። ይሁን እንጂ ህይወት ከባድ በሚሆንበት ግዜ ህይወትን የተሻለ የሚያደርግልን ቡና አይደለም፡፡ ቡና ጥቅም የለውም እያልኩ ሳይሆን የእውነት ህይወት በከበደን ግዜ ህይወትን የተሻለ የሚያደርግልን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እምነት ነው፡፡


ድሮ በጦርነት ግዜ ሰዎች እራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ጋሻ ይጠቀማሉ፡፡ በኤፌሶን 6:16(አመት) ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ተመሳሳይ ነገር፤ እምነትን እንደጋሻ በመጥቀስ ይፅፍልናል፡፡


ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤


የእምነት ጋሻ ከሌለን ማነኛውም ወደኛ የተወረወረ ነገር ያጠቃናል፤ ለዛም ነው የእምነት ጋሻ ያስፈልገናል የምንለው፡፡ እድሜ የሚያስተምረንነገር ቢኖር ሁሉም ነገር ግዜያዊ እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማንነት፤ ቃሉና ኪዳኑ ዘላለማዊ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ መሠረት ያደረገ ትክክለኛና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትን ካለን በትክክለኛ ስፍራ ላይ ነን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በማንነቱ ላይ መሰረት ያደረገ እምነት ይስጠን አሜን፡፡

References
1. Joyce Meyer Daily Devotional
2. https://www.youtube.com/watch?v=swSdOuzWd2Q

የተከፈቱ ጽሑፎች ከመስመር ውጭ ለማንበብ በዚህ መሣሪያ ይቀመጣሉ።